Thursday, December 30, 2010

የሰላምና የእርቅ ጉባኤ

  • በሀገር ውስጥ ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ የሰላምና የእርቅ ጉባኤ አስመልክቶ ስብሰባ አካሔደ።
  • በስደት የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ በቅርቡ ስብሳባ ያካሂዳል።
  • ሁለቱን ሲኖዶሶች በማገናኘት አዎንታዊ ተልእኮውን በመወጣት ላይ የሚገኘው የሰላምና የእርቅ ኮሚቴም መጪውን የሰላምና የእርቅ ጉባኤ ለማስተናገድ በዋሺንግተን ዲሲ ሰሞኑን ስብሰባ ያደርጋል።

በሀገር ቤት የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ የእርቅ ጉባኤን አስመልክቶ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ለዕርቀ ሰላሙ ስብሰባ የሚወክሉትን ሦስት ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስን፣ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስን እና ብፁዕ አቡነ ገሪማን መርጧል። በጸሐፊነት ንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ ከሊቃነ ጳጳሳቱ ጋር ለድርድሩ እንዲጨመሩ ተወስኗል። በመቀጠልም በቅድመ ሁኔታ ደረጃ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ ማዕረጋቸውና ደረጃቸው ተጠብቆ በውጭ ሀገር በፈለጉት ቦታ ተቀምጠው አገልግሎታቸውን እንዲፈጽሙ የተስማማ ሲሆን እንደዚሁም በስደት ሀገር ማዕረገ ጵጵስና የሾሟቸውን የአሥራ ሦስቱን ጳጳሳት ሲመት ለመቀበል ወስኗል።

ይህ በዚህ እንዳለ ሆኖ በስደት ሀገር የሚገኘው ቅዱስ ሰኖዶስ በሀገር ውስጥ ካለው ሲኖዶስ የቀረለበትን ቅድመ ሁኔታ እና የመነጋገሪያ አጀንዳ አጥንቶ ለመወሰንና የራሱን የመነጋገሪያ አጀንዳ ቀርጾ ለሰላም ኮሚቴው ለማቅረብ በቅርቡ ስብሰባ እንደሚያካሂድ ያለን መረጃ ያመለክታል። በስደት የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶሰ እንደ ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ በቤተ ክርስቲያኗ ታሪክ የተከሰተው የቀኖና ጥሰት ከእንግዲህ እንዳይደገም የሚያቀርበው የመፍትሔ ሃሳብ እንዳለ ይጠበቃል።

በሌላ በኩል የማሕበር ቅዱሳን ልሳን የሆነው ደጀ ሰላም በድረ ገጹ ላይ በስደት የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶሰ ለሽማግሌነት አምባሳደር ካሣ እና ፕሮፌሰር ኤፍሬምን መርጧል በማለት እያናፈሰ ያለው ዜና ሐሰት እንደሆነ ለማረጋገጥ ችለናል። በስደት የሚገኙት አባቶች ለስብሰባው የሚመርጧቸውን አደራዳሪዎች ገና እንዳልመረጡ የደረሰን መልእክት ያስረዳል። ከዚህ በተጨማሪ ይኸው ድረ ገጽ በሀገር ቤት ያሉት አባቶች ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ በሀገር ውስጥ በአንድ ገዳም ተወስነው እንዲኖሩ፣ የተቀሩት ሊቃነ ጳጳሳት ደግሞ ሀገር ቤት ተመልሰው ቅዱስ ሲኖዶስ በሚመድባቸው ሥፍራ ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ተወስኗል በማለት ያልተወሰነውን እንደተወሰነ አድርጎ አዛብቶ ያቀረበው ዘገባ የተሳሳተ እንደሆነም አዲስ አበባ ከሚገኙ አባቶች ለመረዳት ተችሏል። በዚህ ያዘኑ የሰላምና የእርቅ ድርድሩን በጉጉት የሚጠባበቁ በእውነትም እንደሚሉት ለዚህ የእርቅ ድርድር መሳካት ፍላጎት ካላቸው ደጀ ሰላማውያን የፈጠራና የተሳሳተ ወሬ ከማቅረብ የተጀመረውን የሰላም ጥረት ለማምከን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ከሚሰነዝረው ዘገባ እንዲቆጠቡ እናሳስባለን ብለዋል።  

በተያያዘ የዜና መረጃችን እንደተረዳነው የሰላምና የእርቅ ኮሚቴው ከሀገር ቤት ሲኖዶስ የተላከውን የመነጋገርያ አጀንዳ አጥንቶ በስደት ለሚገኘው ሲኖዶስ ለማቅረብ፣ የጉባኤውን ቦታና ጊዜ ለመወሰን እንዲሁም ለድርድሩ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ እንዲያስችለው ሰሞኑን በዋሺንግተን ዲሲ ስብሰባውን ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ይገኛል። በደረሰን መረጃ መሠረት የእርቀ ሰላም ስብሰባውን ቦታ በተመለከተ ደጀ ሰላም በዜና መልክ እንደዘገበችው በካይሮ ወይም በኢየሩሳሌም ወይም በናይሮቢ ሳይሆን የሰላምና የእርቅ ኮሚቴው ባለበት በዚሁ በአሜሪካ እንደሚሆን ለመረዳት ችለናል። ያለፈው የእርቀ ሰላም ስብሰባ እንደታሰበው ውጤታማ ያልሆነው በዋሺንግተን ዲሲና በአካባቢው የሚገኙ የቤተ ክርስቲያንና የፖለቲካ ሰዎች በአባቶች ላይ ያሳደሩት ተጽዕኖ እና የነበራቸው ጣልቃ ገብነት ስለሆነ ይህንን ለመቅረፍ ሲባል የአባቶቹ ጉባኤ በዋሺንግተን ዲሲ እንደማይሆን ይጠበቃል።

በአንደበታቸው ብቻ የዚህን እርቀ ሰላም ጉባኤ መሳካት የሚደግፉ ሆኖም ግን በግብራቸው የራሳቸውን ወይም የማሕበራቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚሯሯጡ እንዳሉ በሚገባ እየተስተዋለ ነው። እስከ ዛሬ ድረስ ለመከፋፈሉም፣ ለገለልተኝነቱም ሆነ ለተለያዩ የቤተ ክርስቲያኗ ችግሮች ራሳቸውን ነፃ አድርገው የአባቶችን መለያየት በምክንያት እያቀረቡ ሲያወሩ የቆዩ ብዙዎች ዛሬ አባቶች ለመወያየት ወደ ጠረጴዛ ሲቀርቡ በጸሎትም ሆነ በሚችሉት መንገድ ሁሉ መርዳት ሲገባቸው በብዙ መንገድ መሰናክል ሲያስቀምጡ ይታያል። እግዚአብሔር እንዴት ነው ታዲያ እኛን የሚለመነን?

በሀገር ቤቱ ሲኖዶስ ተሹመው በአሜሪካ የሚያገለግሉት አቡነ አብርሃም እና በዙሪያቸው ያሉ ስብሰቦች ነገሮችን አጣምሞ በማቅረብና አባቶችን በማደናበር ያለፈው የእርቀ ሰላም ስብሰባ እንዳይሳካ ዋነኛ ምክንያት እንደነበሩ የታወቀ ነው። አሁን ግነ ከዚህ ዓይነቱ ተግባር ተገድበው ይልቁንም ስለ ቤተክርሰቲያን አንድነት ሲሉ ለመጪው ስብሰባ መሳካት በግልጽ መጣር ይገባቸዋል። በእሳቸው ሥፍራ የነበሩት አቡነ ማቲያስ ይህ እድል ገጥሟቸው ቢሆን ኖሮ ምንኛ ትልቅ ሥራ በሠሩ ነበር።

ይህ እርቀ ሰላም ለቤተ ክርስቲያናችን ሊያመጣ የሚችለው ጥቅም ለአንዳንዶች ጉዳት ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው። እኛ ሰላም ሊመጣልን ነው ብለን ስንደሰት ሰላም ሊመጣብን ነው ብለው የሚጨነቁ መኖራቸው ያሳዝናል ያሳፍራልም። እኛ ግን እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን ተቆርቋሪዎች ተስፋችንን በፈጣሪያችን አድርገን ይህንን እርቀ ሰላም እግዚአብሔር ከፍሬ እንዲያደርሰው እንጸልያለን። ይህንን የእርቀ ሰላም ጉባኤ ለማስተባበር የሚደክሙትን የሰላምና የእርቅ ኮሚቴ አባላት እግዚአብሔር ውለታቸውን እንዲከፍላቸው እንመኛለን። የጀመሩትን እንዲያሳካላቸው በጸሎት፣ በገንዘብ፣ በእውቀት እና በሚቻለው ሁሉ ማገዝ የእውነተኛ የቤተ ክርስቲያንዋ ምእመናን ድርሻ ነው።      

የቤተ ክርስቲያን አምላክ እግዚአብሔር ቸር ወሬ ያሰማን።


ይትባረክ አምላክ አበዊነ::



3 comments:

  1. thank you for the update

    ReplyDelete
  2. Thanks for fair and balanced report

    ReplyDelete
  3. qale hiwot yasemalehn! Let us all pray for the unity our church.

    ReplyDelete