Thursday, January 6, 2011

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና የአንድነት ጉባኤ መግለጫ አወጣ።

በዚህ ሳምንት ለሁለት ቀናት በሜሪላንድ ስብሰባውን ያካሄደው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና የአንድነት ጉባኤ መግለጫ አወጣ።
  • የድጋፍ ጥሪ ለቤተ ክርስቲያንዋን ምእመናን ካህናት እና ሊቃውንት አስተላልፏል።
  • ለሰላሙ መሳካታ በማይበጁ አስተያየቶች ሕዝቡን ግራ እንዳያጋቡ ለዜና ማሰራጫዎች ጥሪ አቅርቧል።
  • ባዘጋጀው ድረ ገጽ (website) ላይ መረጃ እንደሚያስቀምጥ አስታውቋል።


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ
ታኅሣስ 25 እና 26 በሜሪላንድ ቤተ ሳይዳ ያደረገውን ስብሰባ ሲያጠናቅቅ የተሰጠ
መግለጫ።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

«ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፤ በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን።»
ሐዋርያዊት፣ ጥንታዊት፣ ብሔራዊትና ታሪካዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንደ ታላቅነቷ መጠን ሃይማኖትን ከታሪክና ከሥነ ምግባር፣ ፊደልን ከሥነ ጽሑፍ፣ የሀገር አንድነትን ከነፃነት ጋር ጠብቃና አስጠብቃ ለትውልድ ያስረከበች የነፃነትና የአንድነት አርማ (ተምሳሌት) ሆና የኖረች፣ የአገር ባለውለታ የሆነች ታላቅ ቤተ ክርስቲያን የመሆንዋ ጉዳይ በትክክል በእውነተኛው የታሪክ ማኅደር ተመዝግቦ የሚገኝ ሕያው ታሪክ ነው።

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በየዓረፍተ ዘመኑ ያጋጠሟትን ልዩ ልዩ ችግሮች ተቋቁማ በእግዚአብሔር ኃይል አሁን እስከ አለንበት ዘመን ደርሳለች። ቤተ ክርስቲያኒቱ በጽኑ መሠረት ላይ የታነጸች በመሆኗ ከየአቅጣጫው በነፈሱ ነፋሶች ተገፍታ አልወደቀችም። ጠባቂዋና መሠረቷ ክርስቶስ በመሆኑ በየዘመኑ የገጠሟት ችግሮችን ተቋቁማ በድል አድራጊነት ጸንታ ኑራለች፣ ለወደፊትም ጸንታ ትኖራለች።

በአሁኑ ዘመን በአባቶች መካከል የተፈጠረው መለያያት ያሳሰባቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ ካህናትና ምእመናን የቤተ ክርስቲያንን መለያየት አታሳየን እያሉ ፈጣሪያቸውን ዘወትር በጾምና በጸሎት በኃዘንና በእንባ በመለመን ላይ ናቸው።

በእርግጥ የተፈጠረው መለያየት አሳዛኝ ቢሆንም የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ውድቀቷንና ጥፋቷን የማይወድ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያናችን በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ ያለው ሐዋርያዊ አገልግሎቷ በሚያስደንቅ መልኩ እንዲስፋፋና እንዲጠናከር አድጓል።

ስለሆነም በዘመናችን የተከሰተው መለያየት ተወግዶ ጥንታዊትና ታሪካዊት ቤተ ክርስቲያን፣ ሰላማዊ አንድነቷ ፍጹም ተጠብቆ የሚቀጥለው ትውልድ እንዲረከባት ማድረጉ ታሪካዊ ግዴታና ኃላፊነት በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ በአባቶች ዕውቅናና ሕጋዊ ፈቃድ አግኝቶ ሥራውን ከጀመረ ወራትን አስቆጥል።

በመሠረቱ ለዚህ ጉባኤ መነሻና ምክንያት የሆነው የብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ ዕረፍት ቢሆንም ፈቃደ እግዚአብሔር ሆኖ የቤተ ክርስቲያናችን ችግር ያሳሰባቸውና ሰላሟንና አንድነቷን በጽኑ የሚፈልጉ የቤተ ክርስቲያን ልጆችን ያካተተ ጉባኤ ነው።

ጉባኤው የሰላም ሥራውን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በፈቃደ እግዚአብሔር በርካታ ቁም ነገሮችን አከናውኗል። ከነዚህም ውስጥ የሰላምና አንድነት ጉባኤው በሐምሌ ወር ፪ሺሕ /ም ባካሄደው ጉባኤ አማካይነት 18 ዓመታት በላይ ተለያይተው የቆዩ አባቶች በአንድ ማዕከላዊ ስፍራ ተሳባስበው የሰላም ንግግር እንዲያደርጉ ማስቻሉ ነው።

ምንም እንኳን በዚህ ንግግር ጉባኤው ያቀደውና ያለመው ዓይነት ውጤት ባይገኝም፣ ከጀማሪነቱ አንጻር ተስፋ ሰጭ መሆኑን፣ እራሳቸው ተሳታፊ ልዑካን አባቶች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ይህ ዓይነቱ የሰላምና አንድነት ውይይት ሊቀጥል እንደሚገባውም ጉባኤው ከሁለቱም አካላት አስፈላጊውን ፈቃድና ይሁንታ አግኝቷል።

በመሆኑም ከሁለቱም በኩል ከአባቶች የታየው የሰላም ፍላጎትና የተገኘው በጎ ምላሽ የሰላሙን ቀጣይነት አስተማማኝ አድርጎታል። ለዚሁም ለአባቶቻችን ያለን አክብሮትና አድናቆት በእጅጉ የላቀ ነው። ስለዚህ፦

1/ የቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት እንደ ጥንቱ ተጠብቆ እንዲኖር ሊቃውንት ካህናት፣ ምእመናንና ወጣቶች በሙሉ በጾም በጸሎት እግዚአብሔርን ከልብ እየለመናችሁ ለሰላምና አንድነቱ ስኬታማነት አስፈላጊ በሆነው ነገር ሁሉ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሙሉ ድጋፋችሁን ትሰጡ ዘንድ በእግዚአብሔር ስም በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን።

2/ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የምእመናንን ሐሳብ የሚያዳክም የተዛባ ዜና የሚያሰራጩ አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን ድርጅቶች የማሰናከያ ብዕራቸውን ከቤተ ክርስቲያን እንዲያነሱና ይልቁንም በእውነት ለእውነት በመቆም እውነቱን እንዲመሰክሩ እውነቱንም እንዲጽፉ አጥብቀን እንጠይቃለን።

3/ በመጨረሻም የሰላምና አንድነት ጉባኤው የራሱ የሆነ ድረ ገጽ (web site) ያዘጋጀ በመሆኑ ስለ ሰላሙ ሂደት ትክክለኛውን መረጃ www.eotcpeaceandunity.org በማግኘት የሰላሙን ትክክለኛ መልእክት እንድትከታተሉ የአንድነትና የሰላም ጉባኤው ያሳስባል።

ንጉሠ ሰላም ክርስቶስ የአገራችንንና የቤተ ክርስቲያንን ሰላምና አንድነት ይጠብቅ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ

No comments:

Post a Comment