Wednesday, January 26, 2011

Prayer for Peace in our church in Jerusalem

Please follow the link below for a Prayer for Peace in our church in Jerusalem
ቪዲዮው አዲስ አይደለም። የፍልሰታ ሰሞን በፈረንጆች አቆጣጠር በ2009 የተቀረጸ ይመስላል። ቪዲዮው የሚያሳየው በኢየሩሳሌም ከተማ በምትገኘው ኪዳነ ምሕረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለ ሰላም ጸሎት ሲደረግ ነው። የሠርክ ጸሎትን አያይዞ የተደረገ ሥነ ሥርዓት እንደሆነ ለመረዳት ይቻላል። ቪዲዮው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ከተለያዩ የክርስትና እምነት ተከታዮች ጋር በመሆን ለሰላም መቆሟን የሚያመለክት ነው። በተለይም የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ካህን በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተሳታፊ ሆነው ማየት ትልቅ ነገር ነው። ሊበረታታም የሚገባው እንቅስቃሴ ይመስላል።
ይህ ሁሉ መልካም ሆኖ ሳለ ቤተ ክርስቲያናችን ለዚህ የሰላም ጸሎት ተባባሪ ሆና ስትነሳ አንድ ማድረግ ያለባትን ነገር የረሳች ትመስላለች።  


በፓትርያርክ ላይ ፓትርያርክ መሾሙ ባስከተለው መዘዝ ምክንያት ተለያይተው የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ለራሳቸው ቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት እንደዚህ ሊጸልዩ ይገባ ነበር። በምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን ትስስር ከሌለን ለሌሎች ጋር እንደዚህ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ፍላጎቱና ምኞቱ ካለን መጀመሪያ በቤታችን ሰላም እንዲኖር ብንተጋ የበለጠ ያምርብን ነበር። እግዚአብሔርስ እንዴት ይለመናል? ለዚህ ጸሎት ምላሽ “በመጀመሪያ ሂድና ከወንድምህ ጋር ታርቀህ ና ከዚያ በኋላ ስለ ሌሎች ሰላም የምታቀርበውን ጸሎትህን እሰማለሁ” ብሎ ቢል እንዴት ይፈረድበታል?
እንደውም ባለፈው ዓመት የትንሣኤን በዓል በኢየሩሳሌም ለማክበር ከአሜሪካ ሔዶ የነበረ አንድ የቤተ ክርስቲያን ማሕበር ሁለት ካህናትን ጨምሮ ነበር የተጓዘው። ሆኖም ግን ዛሬ እንደዚህ በቪዲዮ ከተለያዩ ቤተ ክርስቲያናት ከመጡ ካህናት ጋር ሲጸልዩ የሚታዩት አባቶቻችን ከአሜሪካ የሔዱትን አባቶች በጸሎቱም ሆነ በበዓሉ ሥነ ሥርዓቱ ላይ አላሳተፉም። እንደውም ከተጓዥ ቡድኑ ጋር ራቅ ወዳሉ ቦታዎች ለመጓዝ ያልቻሉት አንደኛው አረጋዊ ካህን ለአንድ ቀን ብቻ በገዳም ለመቆየት እንዲፈቀድላቸው ቢጠይቁ ተከልክለዋል። የገዳምን ሥርዓት አጥተውት አይደለም አሳምረው ያውቁታል። እንደውም በዚያው በኢየሩሳሌም ገዳም በነበሩባቸው ዓመታት ብዙዎችን አስተናግደዋል። ለመከልከላቸው የተሰጠው ምክንያት ቢኖር በአዲስ አበባው ሲኖዶስ ሥር ባለመሆናቸው ብቻ ነበር። እኚህ አረጋዊ ካህን አዝነው ተመልሰዋል። አብሮ የሔደውም ምእመን እጅጉን አዝኗል።
አሁን ታዲያ ከእነዚያ ምእመናን አንዳቸው ይህንን ቪዲዮ ቢያዩ ምን ይሉ ይሆን? አስቀድሞ ጸሎቱ በቤታችን ሰላም እንዲኖር መለመን ከዚያ ደግሞ ለሰላም መሣሪያ ሆኖ መገኘት እንደሚያስፈልግ ሳያሳስቡ እንደማያልፉ አምናለሁ። ለዚህም ነው በተደጋጋሚ ሁላችንም በአባቶች መካከል እየተሞከረ ላለው የሰላምና የእርቅ ጥረት ትልቅ ቦታ ልንሰጠው አስፈላጊ እንደሆነ የሚጠቀሰው። በመለያየቱ ምክንያት የተለያየን ደግሞ በሕብረት ወደ ፈጣሪ ጸሎታችንን ልናሰማ ይገባል። “ለምኑ ይሰጣቸሁአል ፈልጉ ታገኙማላችሁ” ያለንን ቸር ፈጣሪያችንን እንደ ሐዋርያት በአንድ ልብ ሆነን ልንማጸነው ያስፈልጋል።

“በአንድ ሃሳብ ተስማሙ ባንድ ልብ ሆናችሁ
ፍቅርና ሰላም እንዲበዛላችሁ...”  

አሁንም እግዚአብሔር ይህንን የመለያየት ዘመን አሳጥሮ የእኛም አባቶች በአንድነት ሆነው ለማየት እንድንችል ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን።      

No comments:

Post a Comment