Friday, January 7, 2011

ጃንሜዳ በሎስ አንጀለስ

እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ 2003 ዓ.ም. የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን በዓለ ጥምቀት በደመቀ ሁኔታ ለማክበር የሎስ አንጀለስ ድንግል ማርያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በከፍተኛ ዝግጅት ላይ ትገኛለች። ይህ በዓል ከኢትዮጵያ ውጭ ለየት ባለና እጅግ በደመቀ ሁኔታ ላለፉት አሥራ አንድ ዓመታት በሎስ አንጀለስ ከተማ ሲከበር ቆይቷል።

በርከት ያሉ ታቦታት ባንድነት ወደ ጥምቀተ ባሕሩ የሚወርዱበት፣ ቁጥራቸው የበዛ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ካህናትን ዲያቆናት እና መዘምራን እንዲሁም ከተለያዩ ክፍላተ ሃገራት የሚመጡ በብዙ ሽህ የሚቆጠሩ ምዕመናን ስለሚገኙበት “ጃንሜዳ በሎስ አንጀለስ” በሚል ቅጽል ስም ይታወቃል።
   
በዘንድሮውም በዓል እንደ ሀገራችን አከባበር ከስድስት ደብራት ታቦታቱ ወጥተው ወደ ጥምቀተ ባሕር በክብር ታጅበው እንደሚሄዱና በዚያም በታወቁ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን መምህራን ሰፊና ጠለቅ ያለ ግንዛቤ የሚሰጥ የወንጌል አገልግሎት እንደሚካሄድ የዕለቱ መርሃ ግብር ይገልጻል።
ከስምንት የማያንሱ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ከሃያ በላይ አብያተ ክርስቲያናት የሚመጡ ካህናት አባቶች፣ መምህራን እና መዘምራን ይገኛሉ ተብሎ በከፍተኛ ጉጉት እንደሚጠበቅ የደረሰን ዜና ያስረዳል። ይህንን በዓል አስመልክቶም ለአራት ተከታታይ ቀናት ከማክሰኞ ጥር 3 እስከ ጥር 6 ቀን 2003 ዓ.ም. “የእግዚአብሔር ድምፅ ከተማይቱን ይጠራታል።” (ትን. ሚክ. 6፥9) በሚል ርዕስ በብፁዓን ጳጳሳትና በታወቁ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የሚመራ መንፈሳዊ ጉባኤም መዘጋጀቱ ታውቋል።
በተጨማሪም በውጭ አገር ተወልደው አድገው በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ለሚገኙ ወጣቶች ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነታቸውን ይበልጥ ተረድተው የወደፊቷን ቤተ ክርስቲያናቸውን ለመረከብ የበቁ እንዲሆኑ የሚያንፅ ልዩ የወጣቶች ፕሮግራም መዘጋጀቱንም ለመረዳት ችለናል።
እግዚአብሔር አምላካችን በዓሉን የበረከት በዓል እንዲያደርገው እየተመኘን ወደ በዓሉ የሚሄዱትን እግዚአብሔር በመንገዳቸው እንዲጠብቅልን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን። በዓሉን ለማዘጋጀት የሚደክሙትን የሎስ አንጀለስ ከተማ ምዕመናን እግዚአብሐየር ሁሉን እንዲያሳካላቸው በጎደለው እንዲሞላላቸው እንጸልያለን።

ከበዓሉ በኋላ ተጨማሪ ዘገባ እንደምናቀርብላችሁ ተስፋ አለን። እስከዚያው ያለፈውን ዓመት የጥምቀት በዓል በጥቂቱ በቪዲዮ ከዚህ በታች ይመልከቱ።

No comments:

Post a Comment