የብፁዕ አባታችንን የአቡነ ዜና ማርቆስን እረፍት ምክንያት በማድረግ በነጸብራቅ መጽሔት ልዩ እትም ላይ ባለፈው ዓመት ከወጡ ጽሑፎች
የቅዱሳን ጻድቃን ሕይወት በፍጹም ሃይማኖት ተመሥርቶ በቅድስና ለእግዚአብሔር የተሰጠ በመሆኑ አምላካቸው እግዚአብሔርም ልዩ ሥራውን የሠራበት፣ ኃይሉን ያሳየበት፣ በረከቱን ያስተላለፈበትና ክብሩንም የገለጠበት ታላቅ ሕይወት መሆኑን መጻሕፍት አምላካውያት በመተባበር ይመሰክራሉ። ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በቅዱሳን ሕይወት በዝቶ የተትረፈረፈውን ይህን አምላካዊ ጸጋ ሲገልጡም “ሰብእ ይቄድሶ ለመካን፥ ወመካን ይቄድሶ ለሰብእ፤ ሰው ቦታን ይቀድሳል፣ ያከብራል፥ ቦታም ሰውን ይቀድሳል፣ ያከብራልም” ብለዋል። በዚህም ቃል መሠረት መላ ሕይወታቸውን ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሰጡት ታላቁ ኦርቶዶክሳዊ የበረከትና የትሩፋት አባት ብፁዕ አባታችን አቡነ ዜና ማርቆስ የረገጡት ቦታ ተቀድሶና ከብሮ፣ የጨበጡት ሁሉ ተባርኮ፣ የተናገሩት ቃል ተሰምቶ እግዚአብሔር ሥራቸውን ፍጹም ስለባረከላቸው የሲያትል መካነ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤልን ፍጹም አከበረው። በመሆኑም በኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክሳውያን ዘንድ ሲያትል የሚታወቀው በቦይንግ ወይም በማይክሮሶፍት ማዕከልነቱ መሆኑ ቀርቶ በታላቁ ሐዋርያ በብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ ሀገረ ስብከትነቱ ሆነ።
ይህንንም ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ሲገልጽ “እስመ ሠምሩ አግብርቲከ ዕበኒሃ፤ ወአክበርዎ ለመሬታ፤ ባሪያዎችህም ድንጋዮችዋን ወድደዋልና፥ መሬትዋንም ፈጽመው አክብረዋልና” (መዝ. 101፥14) ብሏል። በዚህ አጋጣሚ ሳልጠቅስ የማላልፈው ዐቢይ ነጥብ ብፁዕነታቸው በሲያትል ዋሽንግተን ባደረጉት ታላቅ ሐዋርያዊ ጉዞና በዜና አበው ትምህርት ከሦስቱ የቀጰዶቅያ አባቶች መካከል አንዱ በሆነው በቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ (335-395 ዓ.ም) ሐዋርያዊ ተልዕኮ መካከል ያለውን ትሥሥር ነው። ይኸውም ስመ ጥር የነበረው ታላቁ ኦርቶዶክሳዊ ሊቅ ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ ወንድሙን ቅዱስ ጎርጎርዮስን ኑሲስ በተባለችው ትንሽ ከተማ ጳጳስ አድርጎ ሲመድበው “እኔ የምፈልገው ወንድሜ በመንበረ ጵጵስናው ዕውቅናና ማዕርግ እንዲያገኝባት አይደለም። ይልቁንም አስቀድሞ አትታወቅ የነበረችውን ኑሲስን ተገቢውን ዕውቅና ማዕርግ እንዲሰጣት ነው እንጂ” ሲል ተናግሮአል። ስለሆነም የብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ መንበረ ጵጵስና ለመሆን የተመረጠችውና የታደለችው የሲያትል ከተማም ይህ የቅዱሳን አበው ታሪክ ስለተደገመባት ለብፁዕነታቸው ታላቅነት ሕያው ምስክር ነው።
በጣዕመ ትምህርቱና በሁለንተናዊ ሕይወቱ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን መብራት የሆነው ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ “ተዘከሩ መኳንንቲክሙ ዘነገሩክሙ ቃለ እግዚአብሔር፤ ወእንዘ ትሬእዩ ሠናየ ግእዞሙ ወተመሰሉ በሃይማኖቶሙ፤ የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ። የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነት ምሰሉአቸው” (ዕብ. 13፥7) ሲል እንዳስገነዘበው የብፁዕ አባታችን ሁለንተናዊ ሕይወታቸው በሚገባ የተተረጎመና ዘወትርም የሚነበብ ሕያው መጽሐፍ ነው። በመሆኑም የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸው የሆንን ሁላችን ብፁዕነታቸው በቃል ያስተማሩንንና ከመልካሙ የሕይወታቸው መጽሐፍ ያስነበቡንን ሃይማኖታዊ ዓላማና መንፈሳዊ ተግባር ዘወትር ልንከተልና ትተውልን የሔዱትን ታላቅ መንፈሳዊ አደራም እስከ መጨረሻው ድረስ አጽንተን ልንጠብቅ ይገባል።
በተለይም ብፁዕነታቸው በዚህ አስቸጋሪና ፈታኝ ዘመን ክርስትናን በቃል ገልጸው ያስተማሩንና በሕይወትም ተርጉመውና አጉልተው ያሳዩን ታላቅ መንፈሳዊ አባታችን በመሆናቸው መንፈሳዊ በረከታቸውን ያገኙና ጣዕመ ረድኤታቸውንም የቀመሱ ሁሉ “እግዜር በምድር” እያሉ የብፁዕነታቸውን ታላቅነትና ክቡርነት በአንክሮ ይገልጻሉ። እንደሚታወቀው በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳት መጻሕፍት ከመናፍቃን መጻሕፍት ተለይተው የሚታወቁትና መንፈሳውዊነታቸውና ደግነታቸውም የሚረጋገጠው በሦስት ዐበይት መስፈርቶች አማካይነት ነበር። እኒህም ምስክሮች ውኃ፣ እሳትና ድውያን ናቸው። ይኸውም ይታወቅ ዘንድ መጽሐፉን ከውኃ ላይ ይጥሉታል፣ ከእሳት ውስጥ ይጨምሩታል፣ ከድውያን ላይ ያኖሩታል። ከዚያም መጽሐፉ ውኃው ሳያበላሸው፣ እሳቱም ሳይበላው ደኅና ሆኖ ሲገኝ፤ እንዲሁም ሕሙማን በመጽሐፉ አማካይነት ረድኤተ እግዚአብሔር ደርሷቸው ሲፈወሱ የመጽሐፉ ደግነት ይረጋገጣል። ክቡር ዳዊት “አኅለፍከነ ማዕከለ እሳት ወማይ፤ ወአውጻእከነ ውስተ ዕረፍት፤ በሚያቃጥለው እሳትና በሚያሰጥመው ውኃ መካከል በክንፈ ረድኤትህ ጋርደህ፣ በጽላሎተ ረድኤትህ ከልለህ አሳለፍከን፤ ወደ ዕረፍትም አወጣኸን” (መዝ. 65፥12) እንዲል።
በዚህም መሠረት የብፁዕ አባታችን አቡነ ዜና ማርቆስም ደገኛ አባትነት ለዘመናት በብዙ ዓይነት ገድል ተፈትኖ የተረጋገጠ ከመሆኑም በላይ በብፁዕነታቸው ጸሎትና ቡራኬ የተፈወሱና የተጽናኑ ምእመናን ሥፍር ቁጥር የላቸውም። ይህም አምላካዊ በረከት በዓረፍተ ዘመን የማይገታ በመሆኑ ብፁዕነታቸው በሕይወተ ሥጋ ሳሉ ሲያስተላልፉት የነበረው አምላካዊ ጸጋና በረከት ዛሬም በዐጸደ ነፍስ ሆነው ሳይቋረጥ ዘወትር የሚተላለፍ መሆኑ እሙን ነው። መጽሐፍ “ወይእዜኒ ዕበዩ ለክርስቶስ በሥጋየ እመኒ በሕይወትየ ወእመኒ በሞት፣ አሁንም በሕይወትም ብሆን በሞት የተሰጠኝ የእግዚአብሔር ጸጋ ሁልጊዜ ከእኔ ነው።” (ፊል. 1፥20) እንዲል።
በመጨረሻም ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “ዝክረ ጻድቅ ለዓለም ይሄሉ፤ የጻድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል” (መዝ. 111፥6) ብሎ እንደመሰከረው እውነተኛው ኦርቶዶክሳዊ ሐዋርያ ታላቁ አባታችን ብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ ለዘላለም ሕያው በመሆናቸው በቅዱሳን አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ እቅፍ ሆነው ዛሬም ይባርኩናል፣ በጸሎታቸውና በረድኤታቸውም ዘወትር ይራዱናል።
አምላከ ዜና ማርቆስ የብፁዕነታቸውን በረከትና ረድኤት በሁላችን ላይ ያሳድርብን። አሜን!
እግዚአብሔር እንደ እነዚህ ያሉ የበረከትና የረድኤት አባቶችን አያሳጣን እናንተንም ይባርካችሁ ። አሜን !!
ReplyDelete