Monday, March 14, 2011

ስለ "ማኅበረ ቅዱሳን"

"ማኅበረ ቅዱሳን" የሚታዘዘው ለማን ነው?
ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ወቅታዊ ሁኔታና የወደፊት ጣ የሚነጋገር ሁሉ የሚስማማበት አንድ ነገር አለ። ይኸውም "ማኅበረ ቅዱሳን" የቤተ ክርስቲያን አባቶችን በአንድም በሌላም መንገድ በመከፋፈል እራሱን ብቸኛ የቤተ ክርስቲያንዋ ነጻ አውጪ አድርጎ የመመልከቱ ነገር ነው። አንዳንድ ጊዜማ ከማኅበሩ መመሥረት በፊት በቤተ ክርስቲያን ሥራ እንዳልተሠራ፣ እንዳልተደከመባት አድርጎ በድፍረት በመናገር የወጣቱን ክፍል ለማሞኘት ይሞከራል።  
ይህ ማኅበር ፊት የማያሳዩትን በስደት ውጪ ሀገር የሚኖሩትን አባቶች በማቃለልና ሃይማኖት ለዋጮች እንደሆኑ አስመስሎ በማቅረብ ለብዙ ክብር የበቁትን እያንዳንዳቸው ለቤተ ክርስቲያን ከሃምሳ ዓመታት በላይ የደከሙትን አባቶች በመናቅና በማዋረድ ወጣቶች ለአባቶቻቸው አክብሮት እንዳይኖራቸው ሰድቦ በማሰደብ በስደት ባሉባቸው ቦታዎች ሲያሳድዳቸው ተስተውሏል አሁንም እየተስተዋለ ነው። በቅዱሳን ስም ራሱን ለሚጠራ ማኅበር የከበሩትን ማዋረዱ የተመረጡትን መናቁ ስሙ እንደማይገባው የሚያሳይ ነው።
ይህ ብቻ አይደለም። ይኸው ማኅበር በስደት ያለችውን ቤተ ክርስቲያን ሲያሳድድ “ከአዲስ አበባ ሲኖዶስ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የሰንበት ትምህርት ቤት ማደራጃ መምሪያ ሥር የምተዳደር ነኝ” … “ሲኖዶስ አንዲት ናት” … “ከእናት ቤተ ክርስቲያን ጋር መደባለቅ ያስፈልጋል” በማለት በውጪ ያለውን ሕዝብ በመደለል ነው። ሙከራው እንዳሰበው ባይሳካለትም በቂ ጥፋት ለማጥፋት ያገኘውን አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅሟል።
ማኅበሩ እራሱን በአዲስ አበባ ሲኖዶስ ሥር እንደሆነ አድርጎ ቢያቀርብም በምግባሩ ግን እዚያም ያሉትን አባቶች መከፋፈሉና አልታዘዝ ባይነቱ ዓይን እያወጣ ከመጣ ቆይቷል። እስከ አሁን አንዳንዶች በጠቅላይ ቤተ ክህነት የሚገኙ መምሪያ ላፊዎችን አንዳንድ አባቶችን በገንዘብ፣ ሌሎችንም ደካማ ጎናቸውን አሰመልክቶ ምስጢር እንደሚያወጣ በማስፈራራት አፋቸውን ለጉሞ ቆይቷል። የወደፊቱን እግዚአብሔር ያውቃል። እንደሚታወቀው ይህ ማኅበር “አጥፍተሃል” … “ተሳስተሃል” ... “አሁንስ በቃ! ... አልበዛም እንዴ?” የሚለውን ሁሉ “ተሐድሶ ናቸው” በማለት ወይም “ኑፋቄ አስተምረዋል” ብሎ ስም በማጥፋትና አመጽን በማስተባበር ቅን የቤተ ክርስቲያንዋን አገልጋዮች ስም እያጎደፈ ነው። ብዙዎች ጭንቅ ሆኖባቸው የማኅበሩን ድክመት እያወቁ ተሸክመው ባልተማሩ ልጆች እየታዘዙ “ስቀሉ ሲባሉ እየሰቀሉ” “አውርዱ ሲባሉ እያወረዱ” ማኅበሩ ሊያገኝ ከሚገባው በላይ ሥልጣን እንዲኖረው ምክንያት ሆነዋል። 
ያም ሆነ ይህ “ይህቺ ባቄላ ያደረች እንደሆነ አትቆረጠምም” እንደተባለው ወይም “ቁጭ ብለው የሰቀሉትን ቆመን ማውረድ እንዳያቅተን” ተብሎ እንደተተነበየው ዓይነት ነገር እንዳይመጣ ሁሉም ሊያስተውል ይገባዋል።
የወቅቱ የቤተ ክርስቲያን ችግር ማለትም የአባቶች መለያየትን ማኅበሩ የጥፋት ተልእኮውን ለመፈም ተጠቅሞበታል እየተጠቀመበትም ነው::  እንዲያውም ሁለቱንም ሲኖዶሶች በማቃለልና ባለመታዘዝ የማኅበሩን አጀንዳ የሚያካሂዱ ጥቂት አባቶችን እያታለለ ራሱን እንደ ሦሰተኛ አማራጭ እያቀረበ ነው:: ለዚህም ነው በሁለቱ ሲኖዶሶች መካከል ሰላም እንዲወርድ የማይፈልገው የተጀመረውን የሰላም የእርቅ እንቅስቃሴ ለማምከን የሚንቀሳቀሰው። በአባቶች መካከል ሰላምና እርቅ መምጣቱ ለቤተ ክርስቲያን የሚበጅ ሆኖ ሳለ በቤተ ክርስቲያን ሥር ነኝ ለሚለው ለ"ማኅበረ ቅዱሳን" አልዋጥ ማለቱ ማኅበሩ ድብቅና መተልእኮ እንዳለው በግልጽ የሚያሳይ ነው::       

ስለዚህ ማኅበር ጉዳይ ብዙ ማለት ይቻላል። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ግን ከዚህ በታች ያለውን ደብዳቤ ለአንባቢ ለማቅረብ ሲባል እንደ መግቢያ እንዲሆን ብቻ ስለሆነ እዚህ ላይ እናበቃለን። እንደ ማጠቃለያ የምንለው ቢኖር ሁሉም አቅሙንና ደረጃውን ቢያውቅ፣ ሁሉም ድርሻውን እየታዘዘ ቢሠራ፣ ልጆችም ለመረገም በመቸኮል ፈንታ እንደ ልጅነታቸው በአባቶቻቸው እግር ሥር ቁጭ ብለው ተምረው ቢመረቁ እድሜያቸውም የሚረዝም ለቤተ ክርስቲያንም የሚበጅ መሆኑን ነው።

መልካም ንባብ … 


 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 



































 

Tuesday, February 15, 2011

“አእምሩ ከመ ተሰብሐ እግዚአብሔር በጻድቁ፤ እግዚአብሔር በጻድቁ እንደተገለጠ እወቁ።” (መዝ. 4፥3)

የብፁዕ አባታችንን የአቡነ ዜና ማርቆስን እረፍት ምክንያት በማድረግ በነጸብራቅ መጽሔት ልዩ እትም ላይ ባለፈው ዓመት ከወጡ ጽሑፎች

የቅዱሳን ጻድቃን ሕይወት በፍጹም ሃይማኖት ተመሥርቶ በቅድስና ለእግዚአብሔር የተሰጠ በመሆኑ አምላካቸው እግዚአብሔርም ልዩ ሥራውን የሠራበት፣ ኃይሉን ያሳየበት፣ በረከቱን ያስተላለፈበትና ክብሩንም የገለጠበት ታላቅ ሕይወት መሆኑን መጻሕፍት አምላካውያት በመተባበር ይመሰክራሉ። ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በቅዱሳን ሕይወት በዝቶ የተትረፈረፈውን ይህን አምላካዊ ጸጋ ሲገልጡም “ሰብእ ይቄድሶ ለመካን፥ ወመካን ይቄድሶ ለሰብእ፤ ሰው ቦታን ይቀድሳል፣ ያከብራል፥ ቦታም ሰውን ይቀድሳል፣ ያከብራልም” ብለዋል። በዚህም ቃል መሠረት መላ ሕይወታቸውን ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሰጡት ታላቁ ኦርቶዶክሳዊ የበረከትና የትሩፋት አባት ብፁዕ አባታችን አቡነ ዜና ማርቆስ የረገጡት ቦታ ተቀድሶና ከብሮ፣ የጨበጡት ሁሉ ተባርኮ፣ የተናገሩት ቃል ተሰምቶ እግዚአብሔር ሥራቸውን ፍጹም ስለባረከላቸው የሲያትል መካነ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤልን ፍጹም አከበረው። በመሆኑም በኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክሳውያን ዘንድ ሲያትል የሚታወቀው በቦይንግ ወይም በማይክሮሶፍት ማዕከልነቱ መሆኑ ቀርቶ በታላቁ ሐዋርያ በብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ ሀገረ ስብከትነቱ ሆነ። 

ዓመት እንደ ዋዛ


ዓመት እንደ ዋዛ

የቅዱስ ሲኖዶስ
ክብር ግርማ ሞገስ
ጻድቅ ዜና ማርቆስ
ባርኩን በአጸደ ነፍስ።
      
ቀን ሲቆጠር ጊዜ
የመሮጡ አባዜ
ግባ መሬት ምሡ
አፈርን ሳይቀምሱ።

ሳምንት ሁለት ሳምንት ወራት እየበዛ
ያሉ እየመሰለን ዓመት እንደ ዋዛ።
ከእኛ ጋራ ሆነው ዘውትር ስናያቸው
አብረን ውለን አድረን ከቶ ማን ጠግቧቸው።
           
ቅዱስ አባታችን የተዋሕዶ ቤዛ
ዜና ከተለዩን ዓመት እንደዋዛ።
ብሩህ ገጽታዎን ሳናየው ብንቀር
እናት እንደ ሞተው ብሎናል ቅር ቅር።

ሺህ ዓመት ቢቆጠር ፍቅርን ድል አይነሳም
ዜና አባታችንን ምን ጊዜም አንረሳም።
እውነተኛ ባርያ ለጌታ የተገዛ
በቅፉ ካፈሩ ዓመት እንደዋዛ።

ከልጃቸው ከሰባኬ ወንጌል ሽመልስ ተሊላ

Wednesday, January 26, 2011

Prayer for Peace in our church in Jerusalem

Please follow the link below for a Prayer for Peace in our church in Jerusalem
ቪዲዮው አዲስ አይደለም። የፍልሰታ ሰሞን በፈረንጆች አቆጣጠር በ2009 የተቀረጸ ይመስላል። ቪዲዮው የሚያሳየው በኢየሩሳሌም ከተማ በምትገኘው ኪዳነ ምሕረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለ ሰላም ጸሎት ሲደረግ ነው። የሠርክ ጸሎትን አያይዞ የተደረገ ሥነ ሥርዓት እንደሆነ ለመረዳት ይቻላል። ቪዲዮው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ከተለያዩ የክርስትና እምነት ተከታዮች ጋር በመሆን ለሰላም መቆሟን የሚያመለክት ነው። በተለይም የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ካህን በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተሳታፊ ሆነው ማየት ትልቅ ነገር ነው። ሊበረታታም የሚገባው እንቅስቃሴ ይመስላል።
ይህ ሁሉ መልካም ሆኖ ሳለ ቤተ ክርስቲያናችን ለዚህ የሰላም ጸሎት ተባባሪ ሆና ስትነሳ አንድ ማድረግ ያለባትን ነገር የረሳች ትመስላለች።  

Sunday, January 9, 2011

ሰበር ዜና - ከቤተ ክርስቲያን የሰላምና የአንድነት ኮሚቴ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና የአንድነት ኮሚቴ በሜሪላን ከተማ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ አድርጎት በነበረው ስብሰባ ለመጪው የሰላምና የእርቅ ውይይት አስፈላጊ በሆኑ ቅድመ ዝግጅቶች ላይ እንደሚወያይና ውሳኔ እንደሚያስተላልፍ ተጠብቆ ነበር። በዚህም መሠረት የደረሰን ዘገባ እንደሚያመለክተው የእርቅ ውይይቱን ስፍራ እና ጊዜ በተመለከተ ኮሚቴው ጥልቅ ውይይት ካደረገ በኋላ ስብሰባው በአሜሪካን ሀገር ከዐብይ ጾም መግቢያ በፊት እንዲሆን ወስኗል።  ባለፈው ዓመት ተደርጎ በነበረው የእርቅ ስብሰባ ዙሪያ የታዩትን ችግሮችን ለማስወገድ ይቻል ዘንድ ኮሚቴው የስብሰባውን ከተማና ቦታ እንዲሁም የስበሰባውን ጊዜ በዝርዝር እንደማይገለጽ ለመረዳት ችለናል። በአባቶች ስብሰባ ጊዜ ግራ አጋቢና ሃሳብ ከፋፋይ ግለሰቦች ድርሻ እንዳይኖራቸው አስፈላጊው ሁሉ ጥረት እንደሚደረግም የደረሰን ዘገባ ጨምሮ ያስረዳል።

የልደት በዓል ቡራኬ በስደት ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ


ብጹዕ አቡነ መልከጼዲቅ - ሊቀ ጳጳስ
በስደት የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ

Friday, January 7, 2011

ጃንሜዳ በሎስ አንጀለስ

እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ 2003 ዓ.ም. የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን በዓለ ጥምቀት በደመቀ ሁኔታ ለማክበር የሎስ አንጀለስ ድንግል ማርያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በከፍተኛ ዝግጅት ላይ ትገኛለች። ይህ በዓል ከኢትዮጵያ ውጭ ለየት ባለና እጅግ በደመቀ ሁኔታ ላለፉት አሥራ አንድ ዓመታት በሎስ አንጀለስ ከተማ ሲከበር ቆይቷል።

በርከት ያሉ ታቦታት ባንድነት ወደ ጥምቀተ ባሕሩ የሚወርዱበት፣ ቁጥራቸው የበዛ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ካህናትን ዲያቆናት እና መዘምራን እንዲሁም ከተለያዩ ክፍላተ ሃገራት የሚመጡ በብዙ ሽህ የሚቆጠሩ ምዕመናን ስለሚገኙበት “ጃንሜዳ በሎስ አንጀለስ” በሚል ቅጽል ስም ይታወቃል።